፲፯
፩ በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። ፪ ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤ ፫ ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ። ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው ይል ነበር። ፬ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። ፭ አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤ ፮ ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው። ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ ፯ እነዚህም ሁሉ። ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ ብለው ጮኹ። ፰ ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፥ ፱ ከኢያሶንና ከሌሎቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው። ፲ ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ ፲፩ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። ፲፪ ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ፥ አመኑ። ፲፫ በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ሰበከ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያው ደግሞ መጡና ሕዝቡን አወኩ። ፲፬ በዚያን ጊዜም ወንድሞቹ ወዲያው ጳውሎስን እስከ ባሕር ድረስ ይሄድ ዘንድ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስም በዚያው ቀሩ። ፲፭ ጳውሎስን የሸኙት ግን እስከ አቴና አደረሱት፥ እንደሚቻላቸውም በፍጥነት ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ትእዛዝ ተቀብለው ሄዱ። ፲፮ ጳውሎስም በአቴና ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት። ፲፯ ስለዚህም በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር። ፲፰ ከኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢኮችም ከተባሉት ፈላስፎች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር ተገናኙ። አንዳንዶቹም። ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል? አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው። አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል አሉ። ፲፱-፳፩ የአቴና ሰዎች ሁሉና በዚያ የኖሩ እንግዶች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር በሌላ ጉዳይ አይውሉም ነበርና። ፳፪ ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ። የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። ፳፫ የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። ፳፬ ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ ፳፭ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ፳፮-፳፰ ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። ፳፱ እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም። ፴ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ፴፩ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል። ፴፪ የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን። ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት። ፴፫ እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ። ፴፬ አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።