፮
፩ ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ፪ ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ፫ አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ፬ ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ፭ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። ፮ ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል። ፯ አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ ፰ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ፱ ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። ፲ እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ። ፲፩ እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። ፲፪ በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። ፲፫ በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም። ፲፬ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ፲፭ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። ፲፮ በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። ፲፯ እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ። ፲፰ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።