የዮሐንስ ወንጌል
፩
፩ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ፪ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ፫ ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። ፬ በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ፭ ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ፮ ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ፯ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ፰ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ፱ ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። ፲ በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። ፲፩ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ፲፪ ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ፲፫ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ፲፬ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ፲፭ ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። ፲፮ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ፲፯ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። ፲፰ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። ፲፱ አይሁድም። አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። ፳ መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ። ፳፩ እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ። ፳፪ እንኪያስ። ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት። ፳፫ እርሱም። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። ፳፬-፳፮ ዮሐንስ መልሶ። እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ ፳፯ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ፳፰ ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። ፳፱ በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። ፴ አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። ፴፩ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ፴፪ ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። ፴፫ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። ፴፬ እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ። ፴፭ በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ፴፮ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ፴፯ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ፴፰-፵ መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ። ፵፩ ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። ፵፪ እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው። ፵፫ ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው። ፵፬ በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው። ፵፭ ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። ፵፮ ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ። ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው። ፵፯ ናትናኤልም። ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ። መጥተህ እይ አለው። ፵፰ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ። ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ። ፵፱ ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ። ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው። ፶ ናትናኤልም መልሶ። መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው። ፶፩ ኢየሱስም መልሶ። ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው። ፶፪ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።