፲፰
፩ ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ፪ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር። ፫ ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ከካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ። ፬ ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና። ማንን ትፈልጋላችሁ አላቸው። ፭ የናዝሬቱን ኢየሱስን ብለው መለሱለት። ኢየሱስ። እኔ ነኝ አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ፮ እንግዲህ። እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ። ፯ ደግሞም። ማንን ትፈልጋላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። የናዝሬቱን ኢየሱስን አሉት። ፰ ኢየሱስ መልሶ። እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው አለ፤ ፱ ይህም። ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ፲ ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ። ፲፩ ኢየሱስም ጴጥሮስን። ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን? አለው። ፲፪ እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፥ ፲፫ አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ፲፬ ቀያፋም። አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ ይሻላል ብሎ ለአይሁድ የመከራቸው ነበረ። ፲፭ ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ፲፮ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። ፲፯ በረኛ የነበረችይቱም ገረድ ጴጥሮስን። አንተ ደግሞ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን? አለችው። እርሱ። አይደለሁም አለ። ፲፰ ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ፲፱ ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ፳ ኢየስስም መልሶ። እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ፳፩ ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ አለው። ፳፪ ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ። ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን? ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ፳፫ ኢየሱስም መልሶ። ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ሰለ ምን ትመታኛለህ? አለው። ፳፬ ስለዚህ ሐና እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሰደደው። ፳፭ ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። እንግዲህ። አንተ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ አይደለህምን? አሉት። እርሱም። አይደለሁም ብሎ ካደ። ፳፮ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ። በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበረምን? አለው። ፳፯ ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ፳፰ ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም የፋሲካ በግ ይበሉ ዘንድ እንጂ እንዳይረክሱ ወደ ገዡ ግቢ አልገቡም። ፳፱ ስለዚህ ጲላጦስ ወደ ውጭ ወደ እነርሱ ወጥቶ። ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ አላቸው። ፴ እነርሱም መልሰው። ይህስ ክፉ አድራጊ ባይሆን ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር አሉት። ፴፩ ጲላጦስም። እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት አላቸው። አይሁድም። ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም አሉት፤ ፴፪ ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት ሊሞት እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ፴፫ ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው። ፴፬ ኢየሱስም መልሶ። አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው። ፴፭ ጲላጦስ መልሶ። እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል? አለው። ፴፮ ኢየሱስም መልሶ። መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው። ፴፯ ጲላጦስም። እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። ፴፰ ጲላጦስ። እውነት ምንድር ነው? አለው። ይህንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም። ፴፱ ነገር ግን በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን? አላቸው። ፵ ሁሉም ደግመው። በርባንን እንጂ ይህን አይደለም እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።