፯
፩ ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ፪ ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ። ፫ ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥ ፬ ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ። ፭ ፈሪሳውያንም ጻፎችም። ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። ፮ እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች። ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ ፯ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። ፰ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። ፱ እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። ፲ ሙሴ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና። ፲፩ እናንተ ግን ትላላችሁ። ሰው አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥ ፲፪ ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤ ፲፫ ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። ፲፬ ደግሞም ሕዝቡን ጠርቶ። ሁላችሁ እኔን ስሙ አስተውሉም። ፲፭ ከሰው የሚወጡት ሰውን የሚያረክሱ ናቸው እንጂ ከሰው ውጭ የሚገባውስ ሊያረክሰው የሚችል ምንም የለም። ፲፮ የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ አላቸው። ፲፯ ከሕዝቡ ዘንድ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌውን ጠየቁት። ፲፰ እርሱም። እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን? ፲፱ ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና፤ መብልን ሁሉ እያጠራ አላቸው። ፳ እርሱም አለ። ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። ፳፩ ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ ፳፪ ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ ፳፫ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። ፳፬ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ወደ ቤትም ገብቶ ማንም እንዳያውቅበት ወደደ ሊሰወርም አልተቻለውም፤ ፳፭ ወዲያው ግን ታናሺቱ ልጅዋ ርኵስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ተደፋች ፳፮ ሴቲቱም ግሪክ፥ ትውልድዋም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፤ ከልጅዋ ጋኔን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው። ፳፯ ኢየሱስ ግን። ልጆቹ በፊት ይጠግቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምናአላት። ፳፰ እርስዋም መልሳ። አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። ፳፱ እርሱም። ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት። ፴ ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። ፴፩ ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ አሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። ፴፪ ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፥ ፴፫ እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ ፴፬ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና። ኤፍታህ አለው፥ እርሱም ተከፈት ማለት ነው። ፴፭ ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ። ፴፮ ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት። ፴፯ ያለ መጠንም ተገረሙና። ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ።