1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች. 1. ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና። ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ። ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው። ከእናንተ ወጥቶ የጌታ ቃል በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አልተሰማምና፥ ነገር ግን ምንም እንድንናገር እስከማያስፈልግ ድረስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል።